የግልግል ዳኝነት ምንድን ነው?

የግልግል ዳኝነት ባህሪያት እና መገለጫዎቹ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከአገር አገር የተለያየ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀያየር በመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ሊበጅለት አልተቻለም።[1] በመላው ዓለም ተቀባይነት ባገኙ የግልግል ዳኝነት ስምምነቶች(ኮንቬንሽኖች) እና ህጎች ማለትም በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ ንግድ ህግ ኮሚሽን (UNCITRAL) ሞዴል ህግ ላይም ሆነ በተለምዶ የኒውዮርክ ስምምነት እየተባለ በሚጠራው በውጪ አገር የተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎችን እውቅና ለመስጠት እና ለማስፈፀም የተደረገው ስምምነት ላይ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ይህ እንዳለ ቢሆንም የግልግል ዳኝነት ምንነትንና እና አተገባበሩን ለመረዳት ከዚህ በመቀጠል ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማብራራት እንሞክራለን፡፡

የግልግል ዳኝነት፣ ከፍርድ ቤት ውጪ አለመግባባት ከሚፈታባቸው ዘዴዎች አንዱ ነው። የግልግል ዳኝነት፣ ተከራካሪ ወገኖች “ገላጋይ”[2] አልያም ደግሞ “የግልግል ዳኝነት ጉባኤ” ተብሎ በሚጠራ ሶስተኛ አካል ጉዳያቸው ታይቶ እንዲወሰን ሲፈቅዱ የሚከናወን ሂደት ነው። በግልግል ዳኝነት፣ ገላጋዩ ወይም ደግሞ የግልግል ዳኞቹ የሚመረጡት በተዋዋይ ወገኖች አልያም ደግሞ ዳኞቹን እንዲመርጥላቸው ተዋዋይ ወገኖች በመረጡት አካል (ሿሚ አካል) ሲሆን የግልግል ዳኞቹ የሚሰጡት ውሳኔ አስገዳጅ ነው።

ሬድፈርን እና ሀንተር፣ Law and Practice of International Commercial Arbitration በሚለው ስድስተኛ እትም መፅሐፋቸው “የግልግል ዳኝነት ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ በሚከተለው መልኩ ይመልሱታል።

“Arbitration is essentially a very simple method of resolving disputes. Disputants agree to submit their disputes to an individual whose judgment they are prepared to trust. Each puts its case to this decision maker, this private individual—in a word, this ‘arbitrator’. He or she listens to the parties, considers the facts and the arguments, and makes a decision. That decision is final and binding on the parties—and it is final and binding because the parties have agreed that it should be, rather than because of the coercive power of any state. Arbitration, in short, is an effective way of obtaining a final and binding decision on a dispute, or series of disputes, without reference to a court of law (although, because of national laws and international treaties such as the New York Convention, that decision will generally be enforceable by a court of law if the losing party fails to implement voluntarily).”[3]

ትርጓሜውም

የግልግል ዳኝነት በጣም ቀላል የአለመግባባት መፍቻ ዘዴ ነው፡፡ ተፋላሚ ወገኖች ግጭታቸው በሚሰጠው ውሳኔ ሊተማመኑበት ለተዘጋጁ ግለሰብ ሊሰጡት ይስማማሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ጉዳያቸው ለዚህ ገላጋይ ተብሎ ለሚጠራው ውሳኔ ሰጪ ግለሰብ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ግለሰብ፣ ተከራካሪ ወገኖቹን ያዳምጣል፣ ፍሬ ነገሩንና ክርክራቸውን ግምት ውስጥ በማስገበባትም ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ይህ ውሳኔ የመጨረሻ እና አስገዳጅ ነው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ተከራካሪ ወገኖች እንደዛ እንዲሆን ስለተስማሙ እንጂ የአገሪቱ አስገዳጅ ባህሪ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ፣ የግልገግል ዳኝነት፣ ወደ ፍርድቤት ሳይሄዱ አስገዳጅ እና መጨረሻ ውሳኔ የሚያገኙበት ውጤታማ መንገድ ነው (ምንም እንኳን በብሄራዊ ህግ እና እንደነ ኒውዮርክ ስምምነት ባሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት ተሸናፊው ወገን ሳይፈፅም ሲቀር ወደ ፍርድቤት በመሄድ የሚፈፀም ቢሆንም)፡፡

ስለዚህ፣ የግልግል ዳኝነት ተከራካሪ ወገኖች አስገዳጅ ውሳኔ በሚያስተላልፍ በሶስተኛ ወገን እንዲዳኙ የሚያደርጉት ስምምነትን ተከትሎ የሚከናወን የአለመግባባት መፍቻ ዘዴ ነው ሊባል ይችላል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ የግልግል ዳኝነት ትርጉም በየትኛውም ህግ ተፅፎ አናገኘውም። ቀደም ብለው በነበሩት ህጎችም ሆነ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወጣው የግልግል ዳኝነትና የዕርቅ አሰራር ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ትርጉም ሳይሰጠው ታልፏል። የግልግል ዳኝነት ምንነትን ለመረዳት ይበልጥ አዳጋች የሚያደርገው ግን በነዚህ ህጎች ላይ ያለው የቃላት አጠቃቀም መለያየት ነው። ለምሳሌ በእንግሊዘኛው ‘አርቢትሬሽን’ እየተባለ የሚጠራው የግልግል ዳኝነትን አንዳንድ ህጎች ላይ ሽምግልና[4]፣ አንዳንድ ህጎች ላይ የዘመድ ዳኝነት[5]፣ በሌሎች ህጎች ላይ እርቅ[6] እንዲሁም አንዳንድ ህጎች ላይ ግልግል[7] ተብሎ ይጠራል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ህጎች በተለይ የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ህግ በእንግሊዘኛው ‘አርቢትሬሽን’ እያለ የሚጠራው በአማርኛው ደግሞ ‘እርቅ’ እያለ የሚጠራው የግጭት አፈታት ዘዴ የግልግል ዳኝነት ባህሪያት ሳይኖረው ‘አርቢትሬሽን’ ተብሎ በእንግሊዘኛ መጠራቱ የግልግል ዳኝነትን (አርቢትሬሽንን) ምንነት በአግባቡ ለመረዳት እንቅፋት ከሚሆኑት ምክንያቶች ውስጥ ነው።[8] ይህ ከመሆኑ የተነሳም በኢትዮጵያ ፍርድቤቶች ብዥታ እንደነበረ ቀደም ብለው ከሰጧቸው ውሳኔዎች ማየት ይቻላል።[9] የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ላይም ቢሆን ወጥነት የሌለው እና የተሳሳተ የቃላት አጠቃቀም እንደነበረ ከውሳኔዎቹ በግልፅ የሚታይ ነው። ለምሳሌ በከሳሽ ሙከሚል መሐመድ እና በተከሳሽ ሚፍታህ ከድር መካከል በነበረው መዝገብ ላይ የግልግል ዳኝነትን ‘ግልግል’ በማለት የተገለፀ ሲሆን ከዚህ መዝገብ መረዳት እንደሚቻለው የስር ፍርድቤቶች የግልግል ዳኝነትን ‘የግልግል ስምምነት’ እያሉ እንደሚገልፁት፣ እርቅን (ኮንሲልየሽንን) ደግሞ ‘የግልግል እርቅ’ እያሉ እንደገለፁት ያሳያል። እንደዚሁም፣ በከሳሽ መርዕድ ታደሰ ገ/መድህን ህንፃ ስራ ተቋራጭ እና በተከሳሽ ኦክስፎርድ አመልጌትድ ሀ/የተ/የግል/ማ[10] መካከል በነበረው ክርክርም ሰበር ሰሚ ችሎቱ የግልግል ዳኝነትና እና የዘመድ ዳኝነት እያቀያየረ ሲጠቀም ይስተዋላል። እንዲሁም፣ በከሳሽ አቶ መህዲ ሸረፋ እና በተከሳሽ አቶ ሻፊ ሸረፋ[11] መካከል በነበረው ክርክር ዳኞቹ የዘመድ ሽምግልናን፣ የሽምግልና ዳኝነትን፣ የዘመድ ዳኝነትንና የግልግል ዳኝነትን እያቀያየሩ ተጠቅመዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ፣ የግልግል ዳኝነት ምንነት እና የኢትዮጵያ ፍርድቤቶች ግንዛቤ በአግባቡ ለመረዳት እንዲያስችለን በሰበር ሰሚ ችሎቱ የተሰጡ ትርጉሞችን እንመልከት፦

በከሳሽ አቶ ሙከሚል መሐመድ እና በተከሳሽ አቶ ሚፍታህ ከድር መካከል በነበረው ክርክር ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የግልግል ዳኝነትን ከእርቅ[12] እንዴት እንደሚለይ ሲያስቀምጥ እንዲህ ሲል ይተነትናል።

“……….ግልግል የሚባለው የሽምግልና ዘዴ ደግሞ ግራ ቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን በ3ኛ ወገን አቅርበው የግልግል ዳኛው የሚሰጠውን ውሣኔ የሚቀበሉበት መንገድ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 3325-3346 ድረስ የተመለከቱት ድንጋጌዎችና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 315-319 እና 350-357 የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ስለግልግል አደራረግና አፈፃፀም የሚገዙ ናቸው ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ በሕጉ አግባብ የተደረጉ የግልግል ስምምነቶች ሊፈፀሙ የሚችሉ ስለመሆኑ ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 3325-3346 ድረስ የተመለከቱት ድንጋጌዎች በተለይ ሲታዩም የግልግል ስምምነቶች እንደ ልዩ ውሎች ሊታዩ የሚገባ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

…………በግልግል ዳኛ የሚሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 350 እና ተከታዮቹ መሠረት በበላይ ፍ/ቤት በይግባኝ ቀርቦ እስካልተለወጠ ድረስ በመደበኛ ፍ/ቤት የተሰጠ ውሣኔ በሚፈፀምበት ሥርዓት ቀርቦ ሊፈፀም የሚችል መሆኑንም የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 3345/2/ ድንጋጌ ያስገነዝባል፡፡ በመሆኑም በግልግል ዳኛ የሚሰጥ ውሣኔ የመጨረሻ ነው የግልግል ውሉም ውል እንደመሆኑ መጠን በአግባቡ እስከተቋቋመ ድረስ ተዋዋይ ወገኖችን የሕግን ያህል የሚያስገድድ፣ በቃላቸው እንዲታሠሩ የሚያደርግ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 3325ን ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1731 ጋር አጣምረን ስንመለከት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡”[13] (በፀሐፊው የደመቀ)

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ትርጉም ስንመለከት፣ የግልግል ዳኝነት ተዋዋይ ወገኖች አስቀድመው በግልግል ዳኝነት ለመዳኘት በሚያደርጉት ስምምነት ላይ የሚመሰረት ሲሆን የግልግል ዳኞቹ የሚሰጡት ውሳኔም አስገዳጅ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የግልግል ዳኝነት ስምምነት የሚፀና ስለመሆኑና የግልግል ዳኝነት ውሳኔም በይግባኝ እስካልተለወጠ ድረስ አስገዳጅ እና የፀና ስለመሆኑ በተለያዩ መዝገቦች ላይ አፅንኦት ሰጥቷል።[14] በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በፍርድቤት እንደተሰጠ ውሳኔ የሚቆጠር እና ቀጥታ ለአፈፃፀም ፍርድቤት የሚቀርብ ነው፡፡[15]

ከላይ የተገለፀው እንዳለ ሆኖ፥ የግልግል ዳኝነትን ይበልጥ መረዳት የሚቻለው የግልግል ዳኝነት መገለጫዎችን በማየት ነው፡፡ በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ዋና ዋና መገለጫዎችን በመቀጠል እንመለከታለን፡፡

ሀ) የግልግል ዳኝነት በተከራካሪ ወገኖች ነፃ ፍቃድ መሰረት ይቋቋማል።

የግልግል ዳኝነት ጉባኤ ስልጣን የሚመነጨው ከተከራካሪ ወገኖች ስምምነት ነው። ተከራካሪ ወገኖች በመካከላቸው አለመግባባት ከመፈጠሩ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ የሚያደርጉት የግልግል ስምምነት ለግልግል ዳኝነት ጉባኤ ስልጣን የሚሰጥ ሲሆን በተቃራኒው ፍርድቤቶች በግልግል ስምምነቱ በተሸፈነ ጉዳይ ላይ ስልጣን እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ስለዚህ በመርህ ደረጃ የግልግል ዳኝነት የሚመሰረተው በተከራካሪ ወገኖች ስምምነት ነው።

ከላይ የተገለፀው እንዳለ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አስገዳጅ አልያም ደግሞ የተዋዋይ ወገኖችን ፍቃድ የማይጠይቅ የግልግል ዳኝነቶች በህግ ሊጣሉ ይችላሉ።[16] ለምሳሌ የሚከተሉትን ማየት እንችላለን። አንደኛ፤ በአዋጅ ቁጥር 985/2009 የተሻሻለው የህብረት ስራ ማህበራት አዋጅ ቁጥር 147/1991 ‘የክርክር አወሳሰን’ በሚለው በዘጠነኛው ክፍሉ ላይ ያስቀመጠው አስገዳጅ የግልግል ዳኝነት እንዲህ ይነበባል፡-

“ክፍል ዘጠኝ

የክርክር አወሳሰን

46፡ ጉዳዮችን በእርቅ ስለመጨረስ

በዚህ አዋጅ አንቀፅ 49 የተመለከቱት ክርክሮች ለሽምግልና ዳኝነት ከመቅረባቸው በፊት ጉዳያቸው ተከራካሪ ወገኖች በሚመርጡት ሶስተኛ ወገን በእርቅ መታየት አለበት

47፡ ስለሽምግልና ዳኝነት

1) በዚህ አዋጅ አንቀፅ 49 የተመለከቱት የህብረት ስራ ማህበራት ክርክሮች በእርቅ ያላለቁ እንደሆነ ለሽምግልና ዳኝነት ይቀርባሉ

2) ለሽምግልና ዳኝነት የሚመረጡ ሰዎች ቁጥራቸው ሶስት ሆኖ የማያዳሉ እና መልካም ስም ያላቸው ይሆናሉ።

3 የሽምግልና ዳኞቹ ክርክሮቹን የሚሰሙትና ማንኛውም ተግባራት ሁሉ የሚፈፅሙት በፍትሐብሄር ስነስርአት ህግ መሰረት ነው።

…………………….

49፡ ለሽምግልና ዳኝነት ስለሚቀርቡ ክርክሮች

ስለአንድ ማህበር አቋም ስለስራው አካሄድ ወይም ስለስራው አፈፃፀም በተመለከተ በእርቅ ያላለቁ ጉዳዮችን የሽምግልና ዳኞችን፡

1) በአባላት ወይም በቀድሞ አባላትና ወይም በቀድሞ አባላት ወኪሎች ወይም በሞት በተለዩ አባላት መብት ስም ክርክር በሚያቀርቡ ሰዎች መካከል የሚነሳ ክርክር

2) በአባላቱ፣ በቀድሞ አባላት ወይም በአባላት ወይም በቀድሞ አባላት ወኪሎች ወይም በሞት በተለዩ አባላት ወራሾችና በማህበሩ ስራ አመራር ኮሚቴ በማናቸውም ሹም፤ በወኪሉ ወይም በማህበሩ ሰራተኛ መካከል የሚነሳ ክርክር፤

3) በማህበሩ ወይም በስራ አመራር ኮሚቴ ወይም በማንኛውም የቀድሞ የስራ አመራር ኮሚቴ፣ ማንኛውም ሹም፣ ወኪል ወይም ሰራተኛ ወይም የቀድሞ ሹም የቀድሞ ወኪል ወይም የቀድሞ ሰራተኛ፣ ተጠሪው፣ ወራሾቹ ወይም ወኪሎቹ ወይም በሞት በተለዩ የማህበሩ ሹሞች ወኪሎች ወይም ሰራተኞች መካከል የሚነሳ ክርክር፤

4) በአንድ ማህበርና በማንኛውም ሌላ ማህበር መካከል የሚነሳ ክርክር ለማየት ስልጣን ይኖራቸዋል።

52፡ ስለ ፍርድቤት ስልጣን

በዚህ አዋጅ አንቀፅ 47 መሰረት በሽምግልና ዳኝነት የተሰጡ ውሳኔዎች ላይ እንደአግባቡ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም ማህበሩ በክልል የሚገኝ የሆነ እንደሆነ ለክልል ከፍተኛ ፍርድቤት ወይም ማህበሩ ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ በሆነ ከተማ የሚገኝ የሆነ እንደሆነ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ይግባኝ ማቅረብ ይቻላል።” (በፀሐፊው የደመቀ)

ከዚህ አዋጅ መረዳት የሚቻለው የስራ ማህበራትን አስመልክቶ በአንቀፅ 49 ላይ በተዘረዘሩ ጉዳዮች ላይ የሚነሳው ክርክር ወደ ፍርድቤት ከመሄዱ በፊት በግልግል ዳኝነት ማለቅ እንዳለበት ነው። ይህ የግልግል ዳኝነትም በተከራካሪ ወገኖች ስምምነት የሚፈፀም ሳይሆን በአዋጁ በአስገዳጅነት የተቀመጠ ነው። በሌላ አባባል፣ ይህ የግልግል ዳኝነት ተከራካሪ ወገኖች ሲፈልጉ የሚያስቀሩት፣ አልያም ደግሞ ፈልገው የመረጡት አይደለም።

በዚህ ጉዳይ ላይ በከሳሽ አቶ ዳዊት አበበ እና በአንድነት ቁጥር 4 የጋራ መኖሪያ ቤት እና በተከሳሽ አቶ ካሚል ጀማል[17] መካከል በነበረው ክርክር የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት፣ አመልካች ጉዳያቸው በግልግል ዳኝነት ሳይታይ ክሱን በቀጥታ ለፍርድቤት ማቅረባቸው የህግ መሰረት የሌለው ነው ሲል አሰገዳጅ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

ይህንን አዋጅ በ2009 ዓ.ም ላይ ያሻሻለው የህብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 ላይ ግን እርቅ ማድረግ ይችላሉ ተብሎ በፈቃጅነት ነው የተቀመጠው፡፡ የግልግል ዳኝነትንም ቢሆን በእንግሊዘኛው “shall be referred to arbitration” ተብሎ በአስገዳጅነት የተቀመጠ ቢሆንም በአማርኛው ግን “ለሽምግልና ዳኝነት ሊቀርቡ ይችላሉ” በሚል በፈቃጅነት የተፃፈ አንቀፅ ነው፡፡

ከዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ ውጪም በተለያዩ ጊዜያት የወጡ አስገዳጅ የግልግል ዳኝነት ህጎች ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡[18]

ሁለተኛ፤ ሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በአገሮች መካከል የሚደረጉ ሲሆኑ ባለሀብቶች ጉዳዮቻቸው ወደ አለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት እንዲወስዱ የሚፈቅዱ ናቸው፡፡ ስለዚህ በባለሀብትና በአገሮች መካከል የሚደረገው የግልግል ዳኝነት ክርክር ባለሀብቱና መንግስት አስቀድመው በሚያደርጉት የግልግል ስምምነት የተመሰረተ ሳይሆን በአገሮች መካከል በተደረገ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ይህ ስንል ግን የግልግል ዳኝነት ሂደቱም የሚከናወነው ካለ ተዋዋይ ወገኖች ፍቃድ ነው ማለት አይደለም። ምንም እንኳን አስገዳጅ (ፍቃድ የማይጠይቁ) የግልግል ዳኝነቶች ቢኖሩም እነዚህም ላይም ቢሆን የተከራካሪ ወገኖች ፍቃድ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ የዳኞች ምርጫ ላይ እና የስልጣን ወሰን ላይ፣ ገዢ መሰረታዊ እና የሥነ-ሥርዓት ህግ እና የመሳሰሉት የሚወሰኑት በተዋዋይ ወገኖች ፍቃድ እና ፍላጎት ነው፡፡ በመሆኑም የተዋዋይ ወገኖች ፍቃድ የግልግል ዳኝነት ዋና መገለጫ ነው፡፡

ሆኖም፥ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ የተዋዋይ ወገኖች ነፃ ፍቃድ ፍፁማዊ አለመሆኑ ነው። ምንም እንኳን አብዛኛው የግልግል ዳኝነት ሂደት በተከራካሪ ወገኖች ስምምነት የሚወሰን ቢሆንም ግልግል ዳኝነቱ የሚከናወንበት አገር ህግ ሂደቱ ላይ ተፈፃሚ ስለሚሆን ይህ ህግ የሚከለክላቸውና ተከራካሪ ወገኖች በስምምነት የማይቀይሩት አሰራር ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ የእንግሊዝ የ1996ቱ የግልግል ዳኝነት አዋጅ ተከራካሪ ወገኖች ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ወጪውን እኩል እንካፈላለን ብለው አስቀድመው የሚያደርጉት ስምምነት ተፈፃሚነት የለውም።[19]

በኢትዮጵያው የግልግል ዳኝነት እና የእርቅ አሰራር አዋጅም ቢሆን ይህንን ተመላክቷል።

አንቀፅ 10(3)፡

“በዚህ አንቀጽ ንዐስ የተደነገገው ቢኖርም፣ ስምምነቱን በራሱ ለመፈፀም የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ወይም የዚህን አዋጅ አስገዳጅ ድንጋጌዎችን የሚጻረር ሲሆን የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡”

አንቀፅ 29፡

“በዚህ አዋጅ የተደነገጉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ተዋዋይ ወገኖች ጉባኤው ሊከተለው የሚገባውን ሥነ-ሥርዓት በስምምነት ወይም በሶስተኛ ወገን እንዲወሰን ሊስማሙ ይችላሉ።”

በዚሁ አዋጅ በአስገዳጅነት ከተቀመጡ አንቀፆች አንዱ ደግሞ አንቀፅ 41(4) ላይ ያለው ሲሆን የተዋዋይ ወገኖች ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም፣ በብሄራዊ የግልግል ዳኝነት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ተፈፃሚነት ያለው መሰረታዊ ህግ የኢትዮጵያ ህግ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አከራካሪው ጉዳይ በግልግል ዳኝነት ሊፈታ የማይችል ጉዳይ ነው ተብሎ በህግ ክልከላ ሲደረግበት የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ዋጋ አይኖረውም፡፡

ይህንን የነፃ ፈቃድ ሀሳብ ከመቋጨታችን በፊት አንድ ነገር ማለት ያስፈልጋል፡፡ እሱም በፍርድቤትም ቢሆን የተከራካሪ ወገኖች ነፃ ፈቃድ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ነው፡፡ የውጭ ንክኪ (ፎሬይን ኢለመንት) በሚኖርበት ጊዜ ተዋዋይ ወገኖች በየትኛው ሀገር ፍርድቤት እንደሚዳኙ መስማማት ይችላሉ፡፡ ይህም የቦታ ምርጫ (ፎረም ሰሌክሽን) በመባል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ተዋዋይ ወገኖች ከዚህ በዘለለ፣ የዳኞች ምርጫን ጨምሮ በሌሎች የሥነ-ሥርዓት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ማድረግ አይችሉም፡፡

ለ) አስገዳጅነት ባህሪ አለው

ሌላው የግልግል ዳኝነት መገለጫ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ አሰገዳጅ መሆኑ ነው። አስታራቂ በእርቅ ላይ፣ አግባቢ በማግባባት (ሚድየሽን) ላይ ያላቸው ሚና ተከራካሪ ወገኖች ወደ ስምምነት እንዲመጡ ማገዝ ነው፤ የሚያሳልፉት ገዢ ውሳኔም አይኖርም። ከዚህ በተቃራኒ፣ በግልግል ዳኝነት ግን የግልግል ጉባኤው የሚሰጠው ውሳኔ ልክ እንደ ፍርድቤት ውሳኔ ገዢ ነው።

ሐ) የግልግል ዳኝነት ውሳኔ የመጨረሻነት

የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ልምድ እንደሚያሳየው፣ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡ የኒውዮርክ ስምምነትም ይህንን የሚያስረግጥ ሲሆን ውሳኔው ማሻር አልያም አፈፃፀምን መቃወም የሚቻልባቸው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችንም ያስቀምጣል፡፡ በአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት ዘንድ ያለው ልምድም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደነ እንግሊዝና ኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ሀገሮች ላይ በመሰረታዊ የህግ ስህተት ወደ ፍርድቤት ይግባኝ የሚባልባቸው ሁኔታዎችን ይፈቅዳሉ፡፡ 

የግልግል ዳኝነት ከፍርድቤት በምን ይለያል?

የግልግል ዳኝነትን ከፍርድቤት የሚለዩት በርካታ መገለጫዎች አሉት። እነዚህ መገለጫዎችም ሰዎች ጉዳዮቻቸው ከፍርድቤት ይልቅ በግልግል ዳኝነት እንዲፈታ የሚፈልጉባቸው ምክንያቶች ናቸው። ከላይ የተገለፁ መገለጫዎች እንዳሉ ሆነው፣ ከዚህ በታች የግልግል ዳኝነት መገለጫዎች ከፍርድቤት ባህሪያት በማነፃፀር እንመለከታለን። ነገር ግን እነዚህ መገለጫዎች ሁሌም ልክ ናቸው ማለት አይቻልም። የግልግል ዳኝነት ብሄራዊ ሲሆንና ዓለም አቀፍ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንት ሲሆንና ንግድ ነክ የግልግል ዳኝነት ሲሆን፣ እንዲሁም ከአገር አገር የተለያየ ሊሆን ይችላል። እነዚህ የግልግል ዳኝነት ጠቀሜታዎች ተብለው የተዘረዘሩት መገለጫዎች እውነት ሊሆኑ የሚችሉት የግልግል ስምምነቱ በአግባቡ ሲፃፍ ብቻ እንደሆነም ልብ ሊባል ይገባል። የግልግል ስምምነቱ በአግባቡ ካልተፃፈ የግልግል ዳኝነት ሂደቱ እጅግ የተንዛዛ እና ውሳኔውም የማይፈፀም ሊሆን ይችላል።

ሀ) የግልግል ዳኝነት የተለየ እውቀት ባላቸው ዳኞች የሚታይ መሆኑ

በፍርድቤቶት ጉዳዮች የሚታዩት የተለያዩ ጉዳዮችን በአንድ ጊዜ በሚያዩት ዳኞች ነው። አንድ ዳኛ ከውርስ እስከ ውሎች፣ ከግንባታ እስከ ንግድ ጉዳዮች፣ ከአሰሪና ሰራተኛ እስከ ኩባንያ ህግ ጉዳዮች፣ ከዋስትና ሰነዶች እስከ የማጓጓዝ ውሎች፣ በአጠቃላይ በጣም ሰፋፊ የሆኑ ጉዳዮችን ሊያይ ይችላል። ይህ ከመሆኑ የተነሳም በአንድ ጉዳይ ብቻ ጠለቅ ያለ እውቀት ሊኖረው አይችልም።

በግልግል ዳኝነት ግን የግልግል ዳኞቹ የሚመረጡት በተከራካሪ ወገኖች በመሆኑ ተዋዋይ ወገኖች በጉዳዩ ጠለቅ ያለ እውቀት አላቸው የሚሏቸው ሰዎችን ነው የሚመርጡት። የግድ የህግ ባለሙያዎች እንዲሆኑ ስለማይጠበቅም እንደየጉዳዩ ከህክምና፣ ከምህንድስና፣ ከሂሳብ እና ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ተመርጠው እንዲያዩት ሊደረግ ይችላል። ይህ በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ከፍርድቤት በተሻለ መልኩ በጉዳዩ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ሰዎች የሚያዩበት ሂደት ነው። ነገር ግን ተከራካሪ ወገኖች በተለያዩ ምክንያቶች በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ሰዎችን መምረጥ ካልቻሉ ይህ ከላይ የግልግል ዳኝነት መለያ አድርገን ያነሳነው ሀሳብ ልክ አይሆንም።

ለ) ፍጥነት

ፍርድቤቶች የስራ ጫና ስላለባቸው አንድን ጉዳይ አይተው ለመወሰን አመታት ይፈጅባቸዋል፡፡ ከዛም ባሻገር ፍርድቤቶች የይግባኝ ሰርአት የተዘረጋባቸው በመሆናቸው ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኝ እያለ ጉዳዩ እየተንዛዛ እስከ አስርት አመታት እንዲቆይ ሊደረግ ይችላል፡፡ የግልግል ዳኝነት ግን ጉዳዮች ተሎ እንዲያልቁ የሚያስችሉ ባህሪያቶች አሉት፡፡ አንደኛ፣ ዳኞቹ እንደ ፍርድቤት የስራ ጫና የለባቸውም፤ ሁለተኛ፣ ከተከራካሪ ወገኖች ጋር በመነጋገር ሂደቱ እንዲያጥር ማድረግ ይቻላል፤ ሶሰተኛ፣ አብዛኛው ጊዜ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች የመጨረሻ እና ይግባኝ የማይባልባቸው በመሆኑ ወድያውኑ ያልቃሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ የግልግል ዳኝነት ከፍርድቤት ይልቅ ፈጣንና ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም አሁንም ልብ ሊባል የሚገባው ሁሌም እውነት እንዳልሆነ ነው፡፡ አሁን በቅርቡ ኢትዮጵያ ያሸነፈችው የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ጉዳይን (በከሳሽ አይ ሲ ኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ እና በተከሳሽ የኢትዮጵያ መንግስት[20] መካከል በሄግ፣ ኔዘርላንድስ ሲታይ የነበረው እና በመጨረሻዎቹ 2013 ዓ/ም እልባት ያገኘ ጉዳይን) እንኳን ብንወስድ ክሱ የተጀመረው የተባበሩት መንግስታት ቋሚ የግልግል ዳኝነት ፍርድቤት በድረገፁ እንዳወጣው እ.አ.አ 11 ሜይ 2017 ላይ ነው።[21] ይህ ማለት ክርክሩ ተጀምሮ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ 4 አመት ፈጅቷል። ከዚህ በኋላ የሚኖረው የአፈፃፀም ክስም ደግሞ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ የሚታይ ይሆናል።

ሐ) ገለልተኛነት

ገለልተኛነት ሲባል በሁለት መንገድ የሚገለፅ ነው፡፡ አንደኛ፣ የተቋሙ አልያም ደግሞ የዳኞቹ ገለልተኛነትን የሚያመላክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቦታ ገለልተኛነትን የሚያመላክት ነው፡፡

የተቋሙ አልያም ደግሞ የዳኞቹ ገለልተኛነትን ስንመለከት የአንድ አገር ፍርድቤቶች እና ዳኞች በተለይ ከመንግስት ጋር በሚኖረው ማንኛውም ክርክር ላይ በመንግስት ሊዘወሩ የሚችሉ በመሆናቸው ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ፍርድቤቶች ከአስፈፃሚው አካል እጅ ነፃ ያልወጡ ናቸው የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የግልግል ዳኝነት ከማናቸውም ተከራካሪ ወገኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው በመሆኑ በተሻለ መልኩ ነፃ እና ገለልተኛ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ከመንግስት ጋር በሚኖረው ክርክር ብቻ ሳይሆን ከአገሪቱ ዜጋ ጋር በሚኖረው ክርክርም የአከባቢ አድልዎ (ሎካል ቢያዝ) ሊኖር ይችላል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ አንፃር ሲታይ የግልግል ዳኝነት ከማናቸውም ተከራካሪ ወገኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ በተሻለ መልኩ ነፃ እና ገለልተኛ ናቸው ተብለው ይገመታሉ፡፡ ይህ ግምት ግን ሁሌም እውነት ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ ተችዎች በተለይ በኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ላይ አስተያየት የሚሰጡ ምሁራን፣ የግልግል ዳኞቹ ቋሚ ደሞዝ ስለሌላቸው የገቢያቸው ምንጭ ባለሀብቶች የሚያመጡት ክስ በመሆኑ እነዚህን ባለሀብቶችን ለማበረታት ሲባል ያዳላሉ ይላሉ። ሌላው ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ደግሞ ዳኞች በተከራካሪ የሚመረጡ በመሆናቸው እነዚህ ዳኞች ለመረጣቸው ወገን የማያዳሉ ስለመሆኑ ነው። አልበርት ዣን ቫን ደን በርግ ባደረጉት ጥናት በግልግል ዳኞች የተሰጡ የልዩነት ሀሳቦች ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ለመረጣቸው ተከራካሪ ወገን ወግነው የሰጧቸው የልዩነት ሀሳቦች ናቸው ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ የቦታ ገለልተኛነትን ስንመለከት ደግሞ ፍርድቤቶች ቋሚ ስፍራ ያላቸው በመሆናቸው ለአንዱ ወገን ከሌላኛው ወገን ይልቅ ምቹ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያዊ እና ሌላ አገር ላይ ከሚኖር የውጪ ዜጋ ወገን መካከል የሚኖርን ክርክር በኢትዮጵያ ፍርድቤቶች የሚታይ እንደሆነ፣ አንደኛ ኢትዮጵያዊው የትራንስፖርትም ሆነ የሌላ ወጪ የለበትም፣ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የኢትዮጵያ ፍርድቤቶችን ህግና አሰራር ከዛኛው ወገን ይልቅ በተሻለ መልኩ ያውቀዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ በመሆኑም ሂደቱ ለኢትዮጵያዊው የተመቸ በመሆኑ ገለልተኛ አይደሉም ያስብላቸዋል፡፡ የግልግል ዳኝነትን ግን ብናይ ቦታውም ሆነ ተፈፃሚነት ያለው ህግ የሚወሰነው በሁለቱም ወገኖች ስምምነት በመሆኑ፣ ወገኖች ገለልተኛ የሆነ እና ለሁለቱም የሚስማማ ቦታ ይመርጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

መ) ሚስጢራዊነት

በጥቂት ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር የፍርድቤቶች ሂደቶች ለህዝብ ክፍት የሆኑ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ማን ከሰሰ፣ ለምን ተከሰሰ፣ በምንተከሰሰ፣ ምን ብሎ ተከራከረ እና ምን ተወሰነ የሚለው ከህዝብ ሊደበቅ አይችልም፡፡ በግልግል ዳኝነት ግን ሁሉም ነገር ሚስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ክስ ስለመኖሩም ከተከራካሪ ወገኖች ውጪ ሌላ ሰው ላያውቅ ይችላል፡፡ የንግድ ማህበረሰቡም፣ የንግድ ሚስጢሩ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ስለማይፈልግ የግልግል ዳኝነትን ተመራጭ ያደርጋል፡፡

ነገር ግን ይሄ ሚስጢራዊነት በተለይ በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ላይ ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡ በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ከተከራካሪ ወገኖቹ አንዱ (ብዙ ጊዜ ተከሳሽ) መንግስት በመሆኑ እና የዴሞክራሲዊ መንግስት አሰራር ደግሞ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ሊኖርበት ስለሚገባ ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚደረግ ክርክር ትክክል አይደለም የሚል ትችት ይሰነዘራል፡፡ ሌላኛው የግልግል ዳኝነት ሚስጢራዊነት የሚያስተቸው ፕሮፌሰር ዎን “ዘ ካልቸር ኦፍ ኢንተርናሽናል አርቢትሬሽን” በሚለው መፅሐፋቸውም እንደሚሉት የሚስጢራዊነት መጥፎ ገፅታ ጉድፍ የሰሩትን መደበቁ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ስራ እየሰሩ ያሉትንም የሚደብቅ መሆኑ ነው ይላሉ። ይህ የግልግል ዳኝነት አይነት በትላልቅ የኢንቨስትመንት ተቋሞች ላይ የሚደረግ ክርክር በመሆኑ መንግስታት ሲሸነፉ የአገሪቱ የብዙ አመታት በጀት እንዲከፍሉ ሊወሰንባቸው ይችላል፡፡ ከህዝብ ሀብት (በጀት) ይህን ያክል ሀብት ተቆርሶ ለፍርድ ባለመብት በሚሰጥበት ወቅት ህዝብ ማወቅ አለበት ብለውም ይከራከራሉ፡፡ ይህንን ክርክር ተከትሎም የተለያዩ የግልግል ዳኝነት ተቋማት የሥነ-ሥርዓት ደንቦች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ግልፅ እንዲደረግ የሚያስገድድ አንቀፅ ማካተት ጀምረዋል፡፡[25]

ረ) ተፈፃሚነት

በአንድ አገር ፍርድቤቶች የተሰጠን ፍርድ ሌላ አገር ወስዶ ለማስፈፀም በሁለቱም አገሮች መካከል የተፈረመ ፍርዶችን ለማስፈፀም የሚያስችል የእንካ ለእንካ ስምምነት ሊኖር ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ግን ፍርዶችን ማስፈፀም አይቻልም፡፡

የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎችን ለማስፈፀም ግን በዋነኛነት የሚነሳው በውጪ አገር የተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎችን እውቅና ለመስጠት እና ለማስፈፀም የተደረገ ስምምነት (ኒውዮርክ ስምምነት) ነው፡፡ ይህ ስምምነት ፈራሚ አገሮች በውጪ አገር የተሰጠን ውሳኔ እውቅና እንዲሰጡ እና እንዲፈፅሙ የሚያሰገድድ ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ165 አገሮች በላይ ፈራሚ የሆኑበት በመሆኑ ምክንያት በውጪ አገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በነዚህ አገሮች ሊፈፀም ይችላል፡፡ በመሆኑም የግልግል ዳኝነት ውሳኔ የተሻለ ተፈፃሚነት አለው፡፡ ይህንን ስንል ግን ከዕለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ጋር በተያያዘ ብቻ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፤ በብሄራዊ የግልግል ዳኝነት የፍርድቤት ውሳኔዎችና የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች መካከል የአፈፃፀም ልዩነት የለም።


[1] የግልግል ዳኝነት ውሳኔ በብዙ አገሮች ዘንድ የመጨረሻ እና ይግባኝ የማይባልበት ሲሆን በአንዳንዶቹ ዘንድ ደግሞ (ለምሳሌ በእንግሊዝ፣ ናይጀርያ እና በአገራችን ኢትዮጵያ) በተወሰነ መልኩም ቢሆን ይግባኝ የሚፈቀድበት ሁኔታ አለ። ከጊዜ ወደ ጊዜ የመቀያየሩ ሁኔታም ብናይ ከዚህ በፊት የግልግል ዳኝነት ሚስጢራዊ ሲሆን አሁን አሁን ግን በተለይ አለምአቀፍ የኢንቨስትመንት የግልግል ዳኝነት ግልፅነት እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑን ማየት ይቻላል።

[2] በአንዳንድ የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ላይ (ለምሳሌ በጣና ውሀ ጉድጓድ ቁፋሮና ኢንዱስትሪ ሀ/የተ/የግ/ማ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 127459፣ ቅፅ 22) ዳኞቹ ‘ገላጋይ’ የሚለው ቃል ‘አጅዱኬተር’ የሚለውን ቃል ለመግለፅ ተጠቅመውበታል። ሆኖም በገላጋይ እና በግልግል ዳኛ ልዩነት መፍጠር ብዥታ ከመፍጠር የዘለለ ፋይዳ የሌለው በመሆኑና ገላጋይ የሚለው ቃል ‘አርቢትሬተር’ የሚለውን የእንግሊዘኛውን ቃል የሚተካ በመሆኑ አጠቃቀሙም በዚሁ ቢወሰን ጥሩ ነው።

[3] Alan Redfern and Martin Hunter, Law and Practice of International Commercial Arbitration (6th ed, OUP 2015)

[4] ለምሳሌ የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 973/3ን, 1275/1ን, 1473ን, 2271ን እና 3327ን ይመልከቱ።

[5] ለምሳሌ የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 941ን, 945ን, 1765ን, እና 3325-3326ን ይመልከቱ።

[6] ለምሳሌ የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 945ን ይመልከቱ።

[7] ለምሳሌ የፍትሐብሄር ህግ አንቀፅ 941ን, 945ን, 1275ን ይመልከቱ።

[8] Revised Family Code of Ethiopia, Proclamation No. 213/ 2000, Federal Negarit Gazatta, (Extraordinary Issue No. 1/2000, Addis Ababa, 4th July 2000), arts. 82, 119-122, and 266.

[9] ለምሳሌ በከሳሽ ሙከሚል መሐመድ እና በተከሳሽ ሚፍታህ ከድር መካከል በነበረው ክርክር ላይ ሁለቱም ወገኖች አለመግባባታቸውን በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ የፈቱ ሲሆን አለመግባባቱ የተፈታበት ዘዴ ምንድን ነው በሚለው ዙርያ ፍርድቤቶቹ የተለያየ ውሳኔ ሰጥተዋል። በዚህ መዝገብ ላይ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አለመግባባቱ የተፈታበት ዘዴ ዕርቅ ነው ሲሉ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ደግሞ ውሳኔ አስገዳጅ በመሆኑ ዘዴው የግልግል ዳኝነት ነው ሲል ወስኗል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 38794 ቅፅ 9ን ይመልከቱ።

[10] የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 97021

[11] የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 161062 ላይ

[12] እርቅ የሚለው ቃል በዚህ መፅሐፍ በእንግሊዘኛው አጠራር ኮንሲልየሽን ተብሎ የሚጠራውን አለመግባባትን መፍቻ ዘዴን ለመግለፅ ነው፡፡ ይህም የሆነው አዲሱ የግልግል ዳኝነት እና የእርቅ አሰራር አዋጅን ጨምሮ አንዳንድ ህጎች ቃሉን ሰለሚጠቀሙበት ነው፡፡ ሆኖም ፀሀፊው ትክክለኛ ቃል ነው ብሎ አያምንም ምክንያቱም እርቅ የሚለው ቃል ሶስተኛ አስታራቂ ወገን ሰለመኖሩም ሆነ የአስታራቂው የስልጣን ወሰን ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም አይደለም፡፡ እርቅ የሚለው ቃል ሁሉም የእርቅ ሂደቶችን ማለትም “ኮንሲልየሽንን”፣ “ሚድየሽንን” እና “ኔጎሽየሽንን” ሊገልፅ የሚችል ቃል ነው፡፡ ፀሀፊው የአዲስ አበባ የግልግል ዳኝነት ተቋም የሚጠቀምበት “ማስማማት” የሚለው ቃል በተሻለ “ኮንሲልየሽንን” ሊገልፅ ይችላል ብሎ ያምናል፡፡

[13] በከሳሽ አቶ ሙከሚል መሐመድ እና በተከሳሽ ሚፍታህ ከድር፣ የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 38794፣ ቅፅ 9።

[14] ለምሳሌ በከሳሽ መርዕድ ታደሰ ገብረመድህን ህንፃ ስራ ተቋራጭ እና በተከሳሽ ኦክስፎርድ አመልጌትድ ሀ/የተ/የግል/ማ መካከል በመዝገብ ቁጥር 97021፣ ቅፅ 18፤ በከሳሽ አቶ መህዲ ሸረፋ እና በተከሳሽ አቶ ሻፊ ሸረፋ መካከል በመዝገብ ቁጥር 161062፣ ቅፅ 24፤

[15] በከሳሽ ወ/ሮ አለሚቱ ተረፈ እና በተከሳሽ የትግል ፍሬ ልብስ ስፌት ማህበር በመዝገብ ቁጥር 27574 በጥቅምት 26 ቀን 2000 ዓ.ም ላይ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠውንና በቅፅ 7 ላይ የታተመውን ውሳኔ ይመልከቱ፡፡

[16] የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 315 ላይ የግልግል ዳኝነት በህግ የሚጠበቅ ሲሆን ወይም ደግሞ በስምምነት /////// በማለት አስገዳጅ የግልግል ዳኝነት ሊኖር እንደሚችል ያስቀምጣል። አዲሱ የግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር አዋጅ ግን የምጠቁም አንቀፅ አልያዘም። ፕሮፌሰር ጌሪ ቦርን ግን ኢንተርናሽናል አርቢትሬሽን በሚለው መፅሐፋቸው ቅፅ ሶስተ ላይ፣ እነዚህ በህግ በአስገዳጅነት የሚጣሉ የግልግል ዳኝነቶች፣ የግልግል ዳኝነት አይደሉም ይላሉ፡፡ (በመፅሐፉ ገፅ 342 ላይ)፡፡ ይህንንም የሚሉት ከኒውዮርክ ስምምነት አንቀፆችና አንዳንድ ብሄራዊ ህጎች አንፃር ነው፡፡ በኒውዮርክ ስምምነት እውቅና የተሰጠው የግልግል ዳኝነት በተዋዋይ ወገኖች ነፃ ፈቃድ የተመሰረተ የግልግል ዳኝነት በመሆኑ፣ የግልግል ዳኝነት ባህሪ ቢኖረውም በግድ የሚጣል ሂደት የግልግል ዳኝነት ሊሆን አይችልም ይላሉ፡፡

[17] የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 91745 ላይ

[18] ለምሳሌ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘካርያስ ቀንዓ “በግልግል የሚታዩ እና የማይታዩ ጉዳዮች በኢትዮጵያ-የመወያያ ነጥብ” በሚለው እና በኢትዮጵያ የህግ መፅሄት 1987 ዓ.ም ላይ በታተመው ቅፅ 17 በግርጌ ማስታወሻው እንዳስቀመጡት ሐምሌ 14 ቀን 1969 ዓ.ም በወቅቱ ተቀዳሚ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ኃይሉ ይመኑ ባወጡት መመሪያ ቁጥር 2756/ፌ1ሀ/20 መሰረት በኢትዮጵያ በመንግስት የልማት ሥራ ድርጅቶች መካከል የሚነሳ ፍትሐብሄር ክርክር በግድ በግልግል እንዲታይ ተደርጎ ነበር፡፡

[19] የእንግሊዝ የ1996ቱ የግልግል ዳኝነት አዋጅ፣ ክፍል 60።

[20] በከሳሽ አይ ኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ እና በተከሳሽ የኢትዮጵያ መንግስት መካከል በነበረው አለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት ጉዳይ፤ የተባበሩት መንግስታት ቋሚ የግልግል ዳኝነት ፍርድቤት  https://pca-cpa.org/en/cases/153/   

[21] የተባበሩት መንግስታት ቋሚ የግልግል ዳኝነት ፍርድቤት https://pca-cpa.org/en/cases/153/

[25] ለምሳሌ አለምአቀፍ ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ በኢንቨስተርና መንግስት መካከል የሚደረግ የግልግል ዳኝነትን ግልፅነት የሚመለከት የተባበሩት መንግስታት ደንብ (UNCITRAL Rules on Transparency in Treaty-based Investor-State Arbitration, 2014) ላይ የተከራካሪ ወገኖች መረጃ እና የክርክሩ የኢኮኖሚ ሴክተር ወድያውኑ በድረገፅ ላይ እንዲወጣና በሂደትም ክስ፥ የክስ መልስ እና ሌሎች ልውውጦች እንዲለጠፉ እንዲሁም ደግሞ የቃል ክርክሩ በተለየ ሁኔታ ሚስጢራዊ መሆን የሚገባው ካልሆነ በስተቀር ለህዝብ ክፍት ሆኖው እንዲከናወኑ ያስገድዳ። ነገር ግን ይሄ የአሰራር ደንብ ተፈፃሚ የሚሆነው ተከራካሪ ወገኖች አስቀድመው በውል ሲቀበሉት ነው። ሌላው በተመሳሳይ መልኩ የ ትራንስ ፓስፊክ የጋራ ስምምነት (Transpacific Partnership Agreement) እንዲህ የሚል አንቀፅ አካቷል:

“Article 9.24: Transparency of Arbitral Proceedings 1. Subject to paragraphs 2 and 4, the respondent shall, after receiving the following documents, promptly transmit them to the non-disputing Parties and make them available to the public: (a) the notice of intent; (b) the notice of arbitration; (c) pleadings, memorials and briefs submitted to the tribunal by a disputing party and any written submissions submitted pursuant to Article 9.23.2 (Conduct of the Arbitration) and Article 9.23.3 and Article 9.28 (Consolidation); (d) minutes or transcripts of hearings of the tribunal, if available; and (e) orders, awards and decisions of the tribunal.”

Related Posts