የአንድ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ከሆኑ ይህንን ሊያውቁ ይገባል

ቴሌቪዥን እየተመለከቱ እያለ ድንገት አንድ ጥሩ ትርፍ የሚያስገኝ ምቹ አጋጣሚ ቢመለከቱ እና በግልዎ ወይም በቤተሰብ ኩባንያዎ በኩል ቢሰሩት ይህ ያሰቡት ንግድ ብዙ ገንዘብ የሚያመጣ ቢሆንና ምቹ አጋጣሚው በዳይሬክተርነት በሚያገለግሉበት ኩባንያ  የንግድ አላማዎች ውስጥ የሚወድቅ በመሆኑ ይህንን  ዕድል ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለው ያስባሉ? ሕጉ እንደዚ ይላል፤

የሕግ ክልከላ

በአዲሱ የንግድ ሕግ ላይ ከተደረጉ ዋና ዋና ለውጦች ውስጥ አንደኛው ስለ ዳይሬክተሮች በሚመለከተው ክፍል ውስጥ ይገኛል።[1] ከአዲሶቹ ጭማሪዎቸ አንዱ የ ”ዶክትሪን ኦፍ ኮርፕሬት ኦፖርቹኒቲ” ይሰኛል፡፡ ይህ የሕግ ፅንሰ ሃስብ ዳይሬክተሮች ኩባንያቸው ሊጠቀምባቸው  የሚችላቸውን ማንኛውንም ምቹ አጋጣሚዎች/እድሎች ለራሳችው እንዳያደርጉ ይከለክላል።

የአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 320 (ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2) እንዲህ ይነበባል፤

     “ስለጥቅም ግጭት

  1. የአንድ ማህበር ዳይሬክተር ከሚመራው ማህበር ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራሱን ማራቅ አለበት።
  2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተጠቀሰው ክልከላ ማህበሩ ሊጠቀምባቸው ቢችልም ባይችልም በተ ንብረትን፣ መረጃን እና የንግ ልን መጠቀም በተመለከተ ተፈጻሚ ይሆናል። “

ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ እንደምንመለከተው፣ ዳይሬክተሩ ማንኛውንም አይነት የጥቅም ግጭት ሊያመጣ ከሚችል ሁኔታ መራቅ እንዳለበት ነው። ኩባንያው በዳይሬክተሩ በኩል በሚመጣ ዕድል ላይ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል። ይህ ምናልባትም የጥቅም ግጭትን ይፈጥራል፤ በመሆኑም ዳይሬክተሩ እራሱን ማራቅ ይጠበቅበታል።

ኩባንያው በገንዘብም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ዕድሉን መጠቀም አለመቻሉ ለዳይሬክተሩ መከላከያ ሊሆንለት አይችልም። ይኸም ሲባል “ኩባንያው ዕድሉን ሊጠቀምበት የሚችልበት ሁኔታ ላይ ስላልነበረ ዕድሉን ለራሴ ወስጃለሁ” ማለት አይችልም።

በተጨማሪም ይሄ ክልከላ ዳይሬክተሩ በዚያ ኩባንያ ማገልገልገሉን ቢያቋርጥም የሚቀጥል ነው። የአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 320 ንዑስ አንቀጽ 3  አንድ ዳይሬክተር በሥራ ድርሻው ምክንያት ያገኘውን ማንኛውንም አይነት የንግድ ዕድል ወይም መረጃ መጠቀም እንደማይችል ይገልፃል። በሌላ አገላለፅ ዳይሬክተሩ ምቹ ሁኔታውን (ዕድሉን) እንኳንስ ለራሱ ለሦስተኛ ወገን ጥቅምም ቢሆን ማድረግ እንደማይችል  የተከለከለ ነው፡፡

መፍትሔው

ከዳይሬክተሮች የሚጠበቀው ቀላል ነው፤ ኩባንያውን ማሳወቅ እና ኩባንያው በምቹ ሁኔታው (በዕድሉ) ለመጠቀም ካልፈለገ ዳይሬክተሩ ሊጠቀምበት ይችላል።

በአዲሱ የንግድ ህግ አንቀፅ 321 መሰረት ከዳይሬክተሮች የሚጠበቀው የትኛውንም የጥቅም ግጭት ሊፈጥር የሚችል ማንኛውንም አይነት ምቹ ሁኔታ (ዕድል) መግለፅ እና ዳይሬክተሩ ደግሞ  በምቹ ሁኔታው (በዕድሉ) የመጠቀም ፍላጎት  ካለው  ለዳይሬክተሮች ቦርድ ማሳወቅ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኩባንያው በምቹ ሁኔታው (በዕድሉ) ለመጠቀም ፍላጎት ከሌለው ዳይሬክተሩ ለቦርዱ ስለፍላጊቱ በማሳወቅ  ሊጠቀምበበት ይችላል ማለት ነው።


[1] የቀድሞ የንግድ ህግ አንቀጾች 347-367 እና የአዲሱን የንግድ ህግ አንቀጾች 296-336 አንብቡ እና አወዳድሩ። የድሮው የንግድ ህግ 20 ድንጋጌዎችን ሲይዝ አዲሱ ደግሞ 40 ድንጋጌዎችን እንዳካተተ ማየት ይቻላል።

Related Posts